Skip to content

የአገር ኅልውናና ድንበር ቋሚ ናቸው ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
የአገር ኅልውናና ድንበር ቋሚ ናቸው ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ/ም ( August 12, 2018 )

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ላለፉት 10 ዓመታት በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ድንበር አስመልክቶ፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ ያደረገውን ሴራና ደባ በቅርብ እየተከታተለ ለባለ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ እያደረገ በማጋለጥ የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል።

በተለያዩ ጊዚያቶች እንደገለጽነው፤ ሕወሓት ከሱዳን ጋር የሚደራደረው የድንበር ስምምነት ኢትዮጵያ ባልተቀበለችው የቅኝ ግዛት ሠነድ በማስረጃነት በጠቀም በመሆኑ፤ የአገራችንን ጥቅም አሳልፎ የሰጠና ሉዓሏዊነቷን ያስደፈረ የአገር ክህደት ተግባር ነው።
ይህ ርዝመቱ ክ 1600 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋቱ ድግሞ 30 እስከ 40 ኪሌ ሜትር የሆነው ለም የድንበር መሬት በተደጋጋሚ በመሬት ላይ ችካል ለመትክል ያደረጉት ጥረት በሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ ሳይሳካ እንሆ እስክዛሬ መቅረቱ ይታወቃል።

ይሁን እንጅ፣ ምንም እንኳን የ1600 ኪሎ ሜትሩ የድንበር መሬት አስምረው ለሱዳን ለማስረከብ ባይሳካላችውም ከሱዳን ጋር ከሚያዋስኑት በጎንደር ክ/ሃገር ለም የእርሻ መሬቶች መካከል የተወስኑ መሬቶችን መስጠታችው በተደጋጋሚ ተገልጾ ነበር። የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ይህንኑ ክሱዳን ጋር የተደረገውን የድንበር ስምምነት ለማግኝት ለበርካታ ዓመታት ጥረት ሲይደርግ ቆይቶአል።

ይህን የአገርን ጥቅምና ሉዓላዊነትን አሳልፎ የሚሰጠውን የድንበር ስምምነት ማን ነው ኢትዮጵያን ወክሎ የፈረመው የሚለው ጥያቄ በዛን ወቅት በሕዝቡ በስፋት በተነሳበት ጊዜ፣ በወቅቱ የአማራው ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን እንደሆኑ ተደርጎ ህዝቡ እንዲያምንና በዋናነት በሠነድ ላይ የፈረመው ስው እንዳይታውቅ ከፍተኛ ጥረት ተደርጉ ነበር። በዚህም መሠረት፣ አቶ ደመቀ መኮንን እንደፈረሙ በብዙ ሕዝብ ዘንድ እንዲታመን ተደርጎ ቆይቶአል።

እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ፤ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ 3 የእርሻ መሬቶችን አሳልፎ ለሱዳን ለማስረክብ የተፈረመው የመግባቢይ ሠነድ በኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ እጅ ሊገባ ችሏል። ይህ 8 አንቀጾች ያሉት ሠነድ የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያን ወክለው የፈረሙት ሕወሓት እንዳስወራው አቶ ደመቀ መኮንን ሳይሆኑ፤ የፈረሙት አቶ አባይ ፀሐየ መሆናችውን በግልፅ ያሳያል። ሱዳንን ወክለው የፈረሙት ደግሞ የሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው። አቶ ደመቀ መኮንን ምንም ባልዋሉበትና ባላደረጉት ወንጀል ያለአግባብ ሆን ተብሎ እንዲወራና የአማራ ክልል ባለሥልጣን መሬቱን አሳልፎ ለሱዳን እንዳስረከበ ተደርጎ እንዲወስድና የወንጀሉ ዋና አካል የሆኑትን ሕወሓት እና አባይ ፀሐየ ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተፈመ ሴራ ነበር። ይህ የኢትዮጽያን ጥቅም አሳልፎ የሠጠ የመግባቢይ ስነድ የኢትዮጽያ ህዝብ እንድያውቀው ከዚህ መግለጫ ጋር በአባሪነት አቅርበናል።

ይህ በአቶ አባይ ፀሐየ የተፈረመው የመግባቢያ ሠነድ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል፤

በመግባብያ ሠነዱ ላይ በግልጽ የተቀመጡ 3 የእርሻ ቦታዎች አሉ። ከነዚህ መካከል ሁለቱ (2) ማለትም፥ በታማራት ኩባንያ እና ሃሰን ሞሐመድ ቶም የሚባሉት “በውሳኔው መሠረት በአስቸኳይ” ለሱዳን መንግሥት ተላልፈው እንዲሰጡ ይላል። ሦስተኛው (3ኛው) ከማል ኡረኢቢ እርሻን በሚመለከት ግን “ኮሚቴው በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኝለት” በማለት ያሳስባል። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ቦታዎቹ የሱዳን ኩባንያ ስያሜ እንዲሰጣቸው መደረጉን ነው። ሠነዱ እንደሚያረጋግጠው ሁለቱም ፈራሚ ባለስልጣናት በቦታው ድረስ መገኝታችው ይገልፃል።

ይህ የመግባብያ ሠነድ ኢትዮጵያና ሱዳን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1902 እና 1907 የተደረጉትን ስምምነቶች እንደተቀበለች አድርጎ ለማቅረብ ሞክሮል። የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴና በርካታ የታሪክና የሕግ ምሑራን ውድቅ ያደረጉትን ሠነድ በማስረጃነት ማቅረቡ ህውሐት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳደረገው ሁሉ ህጋዊ ባልሆነ ሰነድ ለማስፈፅም የታቀደ ለመሆኑ ያረጋግጣል። በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፤ ቀደምት የኢትዮጵያ መንግሥታት ከላይ የሰፈሩትን ስምምነቶች አስመልክተውም ሆነ የሱዳን መንግሥት በየዘመኑ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ያልተቀበሉ መሆናቸው ግልጽ ነው።

ሌላው በጣም የሚደንቀውና የሴራው እምብርት የሆነው ጉዳይ ደግሞ፤ እነዚህ የተጠቀሱት ስፍራዎች የሚገኙት ሕወሓት በፈጠረው በአማራ ክልል ውስጥ መሆናቸው እየታወቀ ስምምነቱ የፈረመው ግን የትላንቱ የሕወሓት ከፍተኛ ሹም አቶ አባይ ፀሐየ መሆናቸው ነው።
ገና ከጥዋቱ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ለ27 ዓመታት ከፍተኛ ግፍና መከራ በሕዝብና በአገር ላይ የፈጸመው የሕወሓት አመራር፤ ለሕዝብና ለአገር በእውነት ቆመው የታገሉትን ሁሉ ያለ ጥፋታቸው ጥፋተኛ በማስመሰል ያለ ስማችው ስም እየሰጠ በእሥር እንዳሰቃየ ሁሉ፤ በራሱ መንግስት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩትን ጭምር ያላደረጉትን አደረጉ በማለት ሲያስር መቆየቱ የአደባባይ ምሰጢር ነው። በዚህ የሕወሓት መሰሪ ተግባር እንዲጠቁ የተደረጉት አቶ ደመቀ መኮንንም ይዋል ይደር እንጅ ይሄው እውነቱ ዛሬ በአደባባይ ይፋ ለመሆን በቃ። የህወሐት ሹሞች ገና ጫካ እያሉ የገቡት ቃል እነዚህ ከላይ ተጠቀሱትን 3 የእርሻ መሬቶች ብቻ ሳይሆን፤ 1600 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለውን የድንበር መሬት ለማስረከብ እንደነበርና ይህንንም ስምምነት ገና ከጅምሩ ሕወሓትን በመወከል ከሱዳን ጋር ይነጋገሩ የነበሩት አበይ ፀሐየ እንደነበሩ አቶ ገብረመድህን አርአያ በዛን ጊዜ የህወሐት አባል የነበሩ የዚህ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ አባል ለኢትዮጵያ ሕዝብ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህ የድንበር ጉዳይ በህወሓት አመራር ሰጪነት ከተፈጠሩ ውስብስብ የአገራችን ችግሮች አንዱ ቢሆንም ችግሩ ትላንት የተፈጠረ ተብሎ ብቻ የማይታለፍ፣ ዛሬም ከባድ በሆነ ሁኔታ የዜጎችን ነፍስ እየቀጠፈ ያለ ጉዳይ በመሆኑ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁኔታውን በትኩረት እየተከታተለው ይገኛል። በተለይ በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል በኢትዬጵያ ፖለቲካ አይነተኛ የለውጥ አመራር መስጠቱንና መላው ህዝብ በተስፋ አብሯችው መሰለፉን ያልወደዱት ቡድኖች አስቀድመው ከአገር በስተጀርባ የጎነጎኑትን የፖለቲካ ሸፍጥ በመጠቀም ሂደቱን ለማደናቀፍና መሪወቹን ከህዝብ ጋር ላማጋጨት ባለፉት ሁለት ወራት በድንበሩ አካባቢ ግልፅ ጦርነት እንዲከፈት አድርገዋል። በዚህም የበርካታ ወገኖቻችን ህይወት አልፏል። ይህ የብዙ ወገኖቻችንን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ችግር ትኩረት የሚሻና መፍትሄ የሚያስፈልገው አብይ ጉዳይ መሆኑን በአንክሮ ለመግለፅ እንውዳለን።

ዛሬ ከፍተኛ የህዝብ ፍቅርና ድጋፍ በተጉናፀፉ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በዶ/ር አብይ አህመድና ከሳቸው ጋር ባሉት የለውጥ ኃይሎች በፈጠሩት አገራዊ ስሜት የተነሳ፤ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ እንደገና የገነኑበት ወቅት ውስጥ ስለምንገኝ፤ ከጎረቤት አገራት ጋር በሰላም፣በመከባበርና በጋራ አብሮ በተለያዩ ዘርፎች በመሥራት ላይ የአተኮረ ግንኙነት የሚፈጠርበት እንጅ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የማይሰጥበት ወቅት ላይ ነን ብለን እናምናለን። አያይዘንም ይህ ኢትዮጽያንና ኢትዮጽያዊነትን ከፍ ያደረገ ለውጥ በዲሞክራሲ ድል አድራጊነት እንዲጠናቀቅ መላው የኢትዮጽያ ህዝብ ተገቢ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርብን እንገነዘባለን። የጋራችን የሆነችውን ውድ አገራች ኢትዮጽያን ህልውና ዛሬም እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ነቅትን የመጠበቅ የትውልድ አደራ አለብን።

የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በቆራጥ ልጆቿ የከበራል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!